የድህነት ጅራፍ እና የፖለቲካ ትርፍ ፈላጊዎችን “እጅ የሚያሰጥ” ፕሮጀክት
- Category: መጣጥፎች
- Hits: 194
በኢትዮጵያ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን ድህነትና ኋላ ቀርነት ታሪክ ለማድረግ የተቀረፀውን እና ለአገሪቱ ሕዳሴ ታላቅ መሰረት የሚሆነውን የአምስት አመቱ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማሳኪያ እየተተገበሩ ከሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱና ዋናው በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ የሚመደበው የስኳር ልማት ፕሮጀክት ነው፡፡
የስኳር ኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ ቢሆንም ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሬ፣ ከሚፈጥረው የስራ ዕድል እና ልማቱ በሚካሄድባቸው ቆላማ አካባቢዎች የአርብቶ እና አርሶ አደሩን ሕይወት ለመቀየርና ኑሮውን ለማሻሻል ከሚኖረው ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎች አኳያ በኢፌዴሪ መንግሥት ልዩ ትኩረት ተችሮታል፡፡
ከዚህ አኳያ በዕቅድ ዘመኑ የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ለማሟላትና ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የነባር ስኳር ፋብሪካዎች (የወንጂ/ሸዋ እና የፊንጫ) የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቆ በቅርብ ወራት አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ግንባታም በመፋጠን ላይ ነው፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን በተለያዩ የአገሪቷ ክልሎች እየተገነቡ የሚገኙ 10 አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ ሂደትም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ከአዳዲሶቹ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱና ትልቁ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በደቡብ ኦሞ ዞን ሳላማጎና ኛንጋቶም ወረዳዎችን፤ በቤንች ማጂ ዞን ማጂ፣ ሱርማ እና ሜኢኒትሻሻ ወረዳዎችን እንዲሁም በከፋ ዞን ዴቻ ወረዳን አካቶ የሚገነባው ኩራዝ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ነው፡፡ አሁን ልማቱ የተጀመረው በሳላማጎ ወረዳ ሲሆን፣ በቀጣይ በሌሎቹ ወረዳዎችም ይካሄዳል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት በ175ሺህ ሄክታር የሸንኮራ አገዳ መሬት ላይ እያንዳንዳቸው በቀን 12ሺህ ቶን አገዳ መፍጨት የሚችሉ ሦስት የስኳር ፋብሪካዎች እና እያንዳንዳቸው በቀን 24ሺህ ቶን አገዳ መፍጨት የሚችሉ ሁለት የስኳር ፋብሪካዎች በአጠቃላይ አምስት ግዙፍ ፋብሪካዎች ይገነባሉ፡፡
የፕሮጀክቱ ስራ ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እና በባለሙያዎች የተደገፈ የሶሺዮ ኢኮኖሚ፣ የአካባቢ ተፅዕኖና የጤና ሁኔታን አስመልክቶ በቂ ጥናት ከመካሄዱ በተጨማሪ ልማቱ በሚካሄድበት አካባቢ ከሚገኙ ማህበረሰቦች ጋር በመወያየት በፕሮጀክቱ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ተደርሷል፡፡ በጥናቱ መሰረት ፕሮጀክቱ በአካባቢው በመገንባቱ በተለያዩ ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እምብዛም (negligible) መሆኑ ታውቋል፡፡
በፕሮጀክቱ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሕይወት ለመለወጥ የሚያስችል የሰፈራ/መንደር ማሰባሰብ ዕቅድም ተዘጋጅቶ በመተግበር ላይ ነው፡፡ በዚህም የአካባቢው አርብቶ አደር ለስኳር ልማቱ በሚገነባው የመስኖ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ስለሚሆን የእንስሳት ግጦሽና ውሃ ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ ያልተረጋጋ ሕይወትን ከመምራት ይድናል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከልማቱ ጋር በተያያዘ በአካባቢው በሚቋቋሙት የትምህርት፣ የጤና፣ የመገበያያ ስፍራ፣ የወፍጮ፣ የመንገድና የመሳሰሉት የመሰረተ ልማት አውታሮች እና ማህበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይህ ስለሆነም ነው የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ የሚኖረው ፋይዳ በእጅጉ የጎላ ነው ተብሎ የሚታመነው፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት መላውን ሕዝብና ልማታዊ ባለሃብቶችን ከጎኑ አሰልፎ የፀረ ድህነት ትግሉን እያቀጣጠለ እና የሕዝቡን የዘመናት የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄ በየደረጃው እየፈታ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ በተቃራኒው የቆሙና የፖለቲካ ትርፍ እናገኛለን ብለው የተሰለፉ ፀረ ልማት ኃይሎች በአካባቢው የሚካሄደውን ልማት ሆን ብለው ለማደናቀፍ እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የኒኦሊብራል፣ የጠባብነት እና የኪራይ ሰብሳቢ አስተሳሰብን የሚያራምዱ ኃይሎች እኩይ ተልዕኳቸውን ለማሳካትና በአለም አቀፍ ደረጃ ጫና ለማሳደር ከመሯሯጣቸው ባሻገር የደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደሮች ከልማቱ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ በማስመሰልና የቀድሞ አኗኗራቸው እንደሚጠቅማቸው ለማሳመን የማይሳካ ሙከራ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
እነዚህ ፀረ ልማት ኃይሎች እንዳለሙት ያላገኙት የአካባቢው አርብቶ አደር ፕሮጀክቱን የማሳካት ጉዳይ የሞት ሽረት ትግል ነው ብሎ በቁርጠኝነት ከሚንቀሳቀሰው መንግሥት ጎን መሰለፍ ብቸኛውና ትክክለኛው አማራጭ መሆኑን ተገንዝቦ የልማቱ ደጋፊና አጋር መሆኑን በአደባባይ መመስከር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በዚህም ብቻ ሳያበቃ የፕሮጀክቱ መሳካት ከየትኛውም የሌላ አካባቢ ሕዝብ በላይ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ተጠቃሚ እንደሚያደርገው በማረጋገጡ በእነዚህ ኃይሎች በተከፈተው መሰረተ ቢስ ወሬ ሳይደናቀፍ ለልማቱ ስኬት የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ነው፡፡
በኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በሚገነቡት ፋብሪካዎች አማካኝነት ዋና እና መለስተኛ ከተሞች የሚመሰረቱ ሲሆን፣ ስምንት የእርሻ መንደሮች እና ከ20ሺህ በላይ መኖሪያና መኖሪያ ያልሆኑ ቤቶች እንዲሁም ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ይገነባሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የ712 ቤቶች፣ የአንድ ዋና ከተማ፣ የአንድ እርሻ መንደር እንዲሁም ከ6ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የሚያለማ የመስኖ አውታር ግንባታዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
እነዚህ ግንባታዎች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ከመሆናቸው አንፃር በስኳር ኮርፖሬሽን የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም በክልሉ መንግሥት ክትትልና በደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር አስተባባሪነት የአካባቢውን አርብቶ እና አርሶ አደር ወጣቶች በጂንካ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በመስጠት ማስመረቅ ተጀምሯል፡፡ የዚህ ፅሁፍ አዘጋጆች ይህንን ሁኔታ ለመዘገብ በህዳር ወር 2005 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በ750 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እና የ16 ብሔር ብሔረሰቦች የፍቅር መንደር ወደ ሆነችው የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ ጂንካ ተጉዘን ነበር፡፡
በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚገኙ ስምንት ወረዳዎችና ከጂንካ ከተማ በመጀመሪያ ዙር የተመለመሉ 202 አርብቶ እና አርሶ አደር ስራ ፈላጊ ወጣቶች በግንባታ፣ በአናፂነት፣ በመሰረታዊ ብረት ብየዳ፣ በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ በቀለም ቀቢነት እና በፕላስተሪንግ(ልስን) የሙያ መስኮች በጂንካ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የ30 ተከታታይ ቀናት የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ተከታትለው ተመርቀዋል፡፡ በቆይታቸው ወቅትም ስለ ንግድ ሥራ አመራር፣ ስለ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ስለ ምርታማነትና ጥራት ማሻሻያ(ካይዘን) የ30 ሰዓት ተጨማሪ ስልጠና አግኝተዋል፡፡
የአካባቢውን ማህበረሰብ የሙያ ክህሎት በማሳደግ በስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ለማድረግና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ታስቦ የተዘጋጀውን ይህን ስልጠና ያጠናቀቁ አርብቶ እና አርሶ አደር ወጣቶች የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሎካ ውብነህ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የአምስት አመቱ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል ከሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል የኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ዞናቸው የዕቅዱ የልማት ቀጠና የመሆን ዕድል ማግኘቱን ገልፀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የዞኑን አርብቶ አደር፣ አርሶ አደር እና የከተማ ሕዝብ በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ልማቱን ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡
በልማቱ አካባቢ የሚገኙትን አርሶና አርብቶ አደሮችን እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በስፋት በማረጋገጥ በህብረተሰቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት መፍጠርና ፕሮጀክቱ ውጤታማና ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ ትክክለኛ አቅጣጫ መሆኑንም በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡ ስለ ሥልጠናው ቀጣይነት የገለፁት አቶ ሞሎካ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት ሳሉ ለወጣቱ የሰጡትን አደራና ያወረሱትን ራዕይ ለማሳካት በቁርጠኝነት ወደ ስራ እንዲገቡ አሳስበዋል፡፡
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር እና በስኳር ኮርፖሬሽን ቅንጅት በኩራዝ የስኳር ልማት ምክንያት በአካባቢው ቀድሞ ያልነበሩ የተለያዩ የማህበራዊ ተቋማትን እና የመሰረተ ልማት አውታሮችን በመንደር ለተሰባሰቡና ለሚሰባሰቡ የህብረተሰብ ክፍሎች መገንባት መጀመሩን በምረቃው ሥነ ስርዓት ላይ ያመለከቱት ደግሞ በስኳር ኮርፖሬሽን የሕዝብ አደረጃጀት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳመነ ዳሮታ ናቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ለህብረተሰቡ መንገድ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ የአርብቶ እና አርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከል፣ ት/ቤት፣ ጤና ተቋም፣ የሕዝብ የህብረት ሱቅ፣ መጋዘኖች፣ ወፍጮ፣ የእንስሳት ጤና ኬላ እና የመሳሰሉት ማህበራዊ ተቋማት እንዲቋቋሙ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ነው አቶ ዳመነ አክለው ያስታወቁት፡፡ በተጨማሪም በመስኖ የሚታገዙ የእርሻ ማሳዎች ለአርብቶ አደሮች እየተዘጋጁ እንደሆነ የገለፁት ኃላፊው በፕሮጀክቱ ጅምር የግንባታ ሂደት ላይ ጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለሰልጣኞቹ ባስተላለፉት መልዕክትም የዕለቱ ተመራቂዎች በሰለጠኑባቸው የሙያ መስኮች ጠንክረው በመስራት ወደፊት ለሚሰለጥኑ እና በተለያዩ መስኮች ለሚሰማሩ ሌሎች የአካባቢው ወጣቶችና ሴቶች አርአያ መሆን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ አመት በዞኑ ለሚኖሩ ከ7 ሺህ 400 በላይ ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች የስራ እድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 400 የሚጠጉ አርብቶ እና አርሶ አደር ወጣቶች በኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ይሰማራሉ፡፡ በፕሮጀክቱ ከሚሰማሩት ውስጥ ከስኳር ኮርፖሬሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በሦስት ዙር 660ውን ለማሰልጠን ታቅዶ በመጀመሪያ ዙር ሥልጠና 202 ወጣቶችን በተመረጡ ስድስት የሙያ መስኮች ማስመረቅ መቻሉንም የዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊ አቶ አለሙ ወ/ስላሴ ገልፀውልናል፡፡ እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ሰልጣኞቹ በመደበኛ ስልጠና ወቅት ያገኙትን እውቀት በመጠቀምና በተመረቁባቸው ሙያዎች በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በመደራጀት ከስራ ጠባቂነት ተላቀው ስራ ፈጣሪ ለመሆን የሚችሉበትን እውቀት አግኝተዋል፡፡ እኛም ከምረቃው ሥነ ስርዓት በኋላ በትክክልም ሰልጣኞቹ እውቀት መጨበጣቸውን የሚያረጋግጡልንን የእጆቻቸው ፍሬዎች የሆኑ በርካታ የተግባር ሥራዎችን ጎብኝተናል፡፡
ከዚህ ስልጠና የተገኘውን ተመክሮ መሰረት በማድረግ ቀጣይ ሁለት ዙር ስልጠናዎች በዚህ አመት የሚዘጋጁ ሲሆን፣ በሶስት ዙሮች ሰልጥነው ወደ ስራ ከሚሰማሩ 660 ወጣቶች በተጨማሪ ቀደም ብለው በማህበር የተደራጁ ከ700 በላይ ወጣቶች በተያዘው በጀት ዓመት በፕሮጀክቱ የስራ መስኮች ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስልጠናውም በቀጣይ አመታት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡
በቆይታችን ጊዜ ባገኙት ሥልጠና ድህነትን የማሸነፊያ መሳሪያ የታጠቁ ተመራቂዎቹን የማነጋገር ዕድል ገጥሞን ነበር፡፡ መጀመሪያ ቃለ መጠይቅ ለመስጠት የተባበረን ከስልጠናው በቂ እውቀት እንዳገኘ የሚናገረው ኪሌ ካምሲዮ ነው፡፡ ወጣቱ ከሳላማጎ ወረዳ የመጣ የቦዲ ብሔረሰብ ተወላጅ ሲሆን፣ የሰለጠነው በብየዳ ሙያ ነው፡፡ ከዚህ ሙያ ጋር ቀደም ሲል እንደማይተዋወቅ አሁን ግን ማንኛውንም የብየዳ ስራ መስራት እንደሚችል አጫውቶናል፡፡ ይህንን ዕድል ያመቻቸውን መንግሥት አመስግኖ እሱና ጎደኞቹ በቀጣይ ወደ ስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ሲሰማሩ ጠንክረው በመስራት እና ውጤት በማስመዝገብ ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ለመጥቀም መዘጋጀታቸውን በልበ ሙሉነት ነግሮን ተሰነባበትነው፡፡
ሌላኛው ተመራቂ የዳሰነች ወረዳ ተወላጅ ሎኮበር ታምራት በበኩሉ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነና አሁን በሰለጠነበት የአናፂነት ሙያ ቀደም ሲል ምንም አይነት እውቀት እንደሌለው ጠቅሶ ይሁንና ሙያውን ይመኘው እንደነበር አውግቶናል፡፡ ስለ ስኳር ልማቱ ሲናገርም “ይህ ፕሮጀክት በዞናችን በመገንባቱ የልማቱ ተጠቃሚ መሆን ችለናል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት እራሳችንን ጠቅመን ለሌሎች እንድንበቃም ከወዲሁ በማህበር ተደራጅተናል” ብሏል፡፡
ከተመራቂዎቹ ውስጥ 23ቱ ሴቶች በመሆናቸው በቀጣይ የምናነጋግራትን በአይናችን እያማተርን ሳለን በድንገት ህፃን ልጅ የታቀፈች ወጣት ተመራቂ ላይ የሁላችንም ቀልብ አረፈ፣ የ18 ዓመቷ ብርሃነሽ ገልጡና ኦልጎ ላይ፡፡ ወጣቷ የቦዲ ብሔረሰብ ተወላጅ ስትሆን ለስልጠና የመጣችው የስኳር ልማቱ ከሚካሄድበት የሳላማጎ ወረዳ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በታች የሆነ ህፃን ይዛ ለወር የሰለጠነችበትን የግምበኝነት ሙያ በንድፈ ሃሳብና በተግባር ስለተማረችው ዕውቀት ከመጨበጥ ባለፈ ሙያውን እንደወደደችው ትናገራለች፡፡ ወደፊትም ጠንክራ በመስራት ቤተሰቧን፣ አካባቢዋን ብሎም አገሯን በልማት የመለወጥ ሃሳብ እንዳላት እና ለዚህም ከወዲሁ በማህበር መደራጀትዋን አጫውታናለች፡፡
በመቀጠል ቆይታ ያደረግነው እንደ ብርሃነሽ ከሳላማጎ ወረዳ ከተመለመለችው የዲሜ ብሔረሰብ ተወላጅ ብዙአለም ወንድወሰን ኡሜ ጋር ነበር፡፡ የ22 ዓመቷ ብዙአለም ከዚህ በፊት የግንበኝነት ሙያን ለመማር ትፈልግ ነበር፤ የአጋጣሚ ነገር ሆነና ይህ ዕድል ሲመጣ ከወረዳዋ ተወዳድራ ለስልጠናው አለፈች፡፡ ወደ ጂንካ ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ከመጣች በኋላም አስቀድማ ትሻው በነበረችው ሙያ ሰልጥና ተመርቃለች፡፡ በመጨረሻም ስለ ስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ምን አስተያየት አለሽ? የሚል ጥያቄ ሰንዝረንላት “ፕሮጀክቱ በአካባቢያችን መገንባቱ ለወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠረ ነው፤ ከዚህ ባሻገር በአካባቢያችን እንደ መንገድ፣ ንፁህ መጠጥ ውሃ፣ ት/ቤት፣ ጤና ተቋማት እና ሌሎች አገልግሎቶች እየተስፋፉ ስለሚመጡ የእነዚህ ሁሉ ተጠቃሚ እንሆናለን፤ አሁንም በልማቱ መሳተፍ እና መጠቀም ጀምረናል” ብላናለች፡፡ ይህች ብሩህ ተስፋን የሰነቀች ወጣት በችግር ምክንያት ከ8ኛ ክፍል ያቋረጠችውን ትምህርት ቀን እየሰራች በምታገኘው ገንዘብ ማታ ለመቀጠል ማቀዷን ስትገልፅልን ፍላጎቷን በማድነቅ መልካም ዕድል ተመኝተንላት ቃለ ምልልሳችንን አበቃን፡፡
በምረቃው ሥነ ስርዓት ላይ አስተያየት ለመስጠት ወደ መድረክ ከወጡት የዞኑ ነዋሪዎች መካከል የሙርሲ ብሔረሰብ ተወላጅ አቶ አሊሳራሊ ኦሊቡይ ይገኙበታል፡፡ እንደ እሳቸው አገላለፅ መንግሥት የአካባቢውን ወጣቶች አሰልጥኖ በስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ለማሰማራት እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ በጣም ደስተኛ ናቸው፡፡ አክለውም “እባካችሁ የደቡብ ኦሞ አካባቢን ለመለወጥ የጀመራችሁትን ስልጠና ቀጥሉበት፡፡ በአካባቢያችን ልማት እንፈልጋለን፤ ስለሆነም ሁላችንም መተባበር፣ አንድ መሆን እና በጋራ መስራት አለብን፡፡ ይህን ካደረግን ደግሞ በፍጥነት እናድጋለን” ብለዋል፡፡ ሌሎችም የጂንካ ከተማ የአገር ሽማግሌዎች የአቶ አሊሳራሊ ሃሳብን በመጋራት ለልማት የተነሳሱትን ተመራቂዎች “ድህነትን ለመዋጋት ከቆረጣችሁ የድል ውጤታችሁን በቅርብ ጊዜ እንደምናይ አንጠራጠርም” በማለት አበረታተዋቸዋል፡፡
አሁን ተመራቂ ወጣቶቹም ሆኑ የአካባቢው ሕዝብ የኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት አሳታፊነቱን እና ጠቀሜታውን በሚገባ ተረድተው እና የልማት አላማ አንግበው ለፕሮጀክቱ ስኬት በባለቤትነት ስሜት ተነስተዋል፡፡
የአካባቢው ለውጥ የማያስደስታቸው አንዳንድ ለሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው የሚቀርቡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ “የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን” ባዮች እና የእነሱን መሰረት የለሽ የፀረ ልማት ዘመቻ የሚያራግቡ የሚዲያ ተቋማት እና ድረ ገፆች በአካባቢው ልማቱ በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝ እና የዞኑ ተወላጆችም የልማቱ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸው ባይዋጥላቸውም ለውጡን በአግራሞት እየተመለከቱት ይገኛሉ፡፡
የአሁኑ ስልጠና የእነዚህን ኃይሎች የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ያከሸፈ እና የልማታዊ መንግሥት ዕቅድ ምን ያህል ወጣቱን እያሳተፈ እና ተጠቃሚ እያደረገ እንደሆነ በትክክል ያረጋገጠ ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም በጂንካ ከተማ የአርብቶ አደሮች ቀን ሲከበር የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ እንደተናገሩት ከዚህ በኋላ አርብቶ አደሩ የአንትሮፖሎጂ ምሁራን የምርምር አጀንዳ እና የጎብኚዎች የካሜራ ሰለባ ብቻ ሆኖ ከሚቀርበት አጋጣሚ ተላቆ የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ወደሚሆንበት ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ ስለሆነም የድህነት ጅራፍ ዳግመኛ እንዳይገርፈው በቁርጠኝነት የተነሳው የልማት ሰራዊት የክቡር አቶ መለስ ዜናዊን ራዕይ እንዲያሳካ ከክልሉ መንግሥት፣ ከዞኑ አስተዳደር እና ከባለድርሻ አካላት ቀጣይ ክትትልና ድጋፍ ይጠበቃል፡፡ በዚህ መልክ የተቀናጀ ጥረት ሲደረግ የድህነት ጅራፍ መጋረፉን ያቆማል፤ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በአፍራሽ ተልዕኮ የተሰለፉ ኃይሎችም ዝም ይላሉ!

